ዜና

አፋውሥኮድ 10ኛ ዓመቱን ሊያከብር ነው

የአፋር ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት /አፋውሥኮድ/ የተመሠረተበትን 10ኛ ዓመት ለማክበር አስፈላጊውን መሰናዶ እያደረገ መሆኑን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ አዚዝ መሀመድ ለሲፋኔ ዜና መጽሔት እንዳስታወቁት ድርጅቱ  ከተመሰረተ 2008 የበጀት ዓመት አሥር ዓመት ሞልቶታል፡፡

በመሆኑም የድርጅቱን የአሥር ዓመት ጉዞ የሚዘክር ዘጋቢ ፊልም፣ መጽሔት፣ ፕሮጀክት ካላንደር እና የአሥር ዓመት ጉዞውን ውጣ ውረዶችና ስኬቶችን የሚያስገነዝቡ መረጃዎች እየተዘጋጁ ናቸው፡፡

በተያዘው ዓመት ውስጥ በሚከበረው የድርጅቱ 10ኛ ዓመት የድርጅቱን አመሠራረትና አሁን የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ የሚያሣዩ ጥናታዊ ጹሁፎች ይቀርባሉ፡፡

ለደርጅቱ ስኬታማነት የነበሩ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች በጥናታዊ ጹሁፍ የሚዳሰሱ ሲሆን የበዓሉ ታዳሚዎች እንዲወያዩበት እንደሚደረግ አቶ አዚዝ ገልፀዋል፡፡

ድርጅቱ በአሥር ዓመት ጉዞው በክልሉ አምስቱም ዞኖች በሚገኙ ከፍተኛ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር በነበረባቸው ወረዳዎች ዘልቆ በመግባት የህብረተሰቡን የንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር  ለመፍታት  ጥረት በማድረጉ የድርጅቱ መልካም ሥራ በክልሉ 32ቱም ወረዳዎች እየታወቀ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

የድርጅቱ ተቀባይነት እየጎለበተ በመምጣቱ ከፍተኛ የውሃ ችግር ባለባቸው ወረዳዎች በአርብቶ አደሩ ዘንድ እንደአለኝታ እየታ§ መምጣቱንም አቶ አዚዝ አስገንዝበዋል፡፡

ድርጅቱ በአሥር ዓመት ጉዞው ከ200 በላይ የንፁህ መጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ ግንባታና የመስመር  ዝርጋታ ሥራ እንዲሁም የመስኖ ልማትና የመንገድ ግንባታዎችን አከናውኗል፡፡

በዞን አምስት የኩማሜ ከተማን በዞን አራት የቴሩ ከተማንና በከተሞቹ አካባቢዎች ያሉ የገጠር ቀበሌዎችን ንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር በመፍታት ረገድ ድርጅቱ የማይተካ ሚና ተጫውቷል፡፡

የኩማሜና ቴሩ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ለመሥራት በርካታ የሥራ ተቋራጮች ሊደፍሩ ያልቻሉትን ደፍሮ በመግባት ህብረተሰቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ ማድረጉ በአሥር ዓመት ጉዞው በአብነት የሚጠቀስ የስኬት ተግባር ነው ያሉት አቶ አዚዝ፤ ባለፉት አሥር ዓመታት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማጎልበት የተሻለ ሥራ ለመሥራት የድርጅቱ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሁሉም ድጋፍ ሰጪ ሠራኞች እጅ እና ጓንት ሆነው እደሚሠሩ አስታወቃዋል፡፡

 

የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግራቸው በአፋውሥኮድ እንደሚፈታ ነዋሪዎች ገለጹ

ለበርካታ ዓመታት የቆየው የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግራቸው በአፋውሥኮድ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው የገዋኔ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል ወ/ሮ አስያ አህመድ፣ ከዲጃ ሁመድ እና ፋጡማ ዓሊ ለሲፋኔ ዘጋቢ እንደገለጹት የከተማዋ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር ከአሥራ አምስት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡

የከተማዋን ንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት በርካታ ተቋራጮች በተለያዩ ጊዜያት ሥራ እየጀመሩ እያቋረጡ መሄዳቸውን ነዋሪዎቹ አስታውሰው፤አፋውሥኮድ በተያዘው የበጀት ዓመት የሁለት የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖች ግንባታና የውሃ መስመር ዝርጋታ እያካሄደ በመሆኑ ለዓመታት የዘለቀው ችግራቸው እንደሚፈታ እምነት አድሮባቸዋል፡፡

አፋውሥኮድ እንደ ገዋኔ የከፋ የውሃ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ውሃ እንዲያገኙ ማስቻሉን ስንሰማ ነበር ያሉት ነዋሪዎቹ፤ግንባታው ለአፋውሥኮድ መሰጠቱን ከሰሙ ጀምሮ መደሰታቸውንና የሥራ አፈፀፃሙም በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የገዋኔ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት  መሀንዲስ አቶ አኑዋር መሀመድ በበኩላቸው  እያንዳንዳቸው  አንድ ሚሊዮን ሊትር ውሃ የመያዝ አቅም ያላቸው ሁለት የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖች ግንባታና ዘጠኝ ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

የገዋኔ ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር በተያዘው የበጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ እንደሚፈታ የተናገሩት አቶ አኑዋር፤ግንባታው ሲጠናቀቅ ከ68 ሺህ በላይ የገዋኔ ከተማና አካባቢው ሕዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

የገዋኔ   ከተማ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት  ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት  በባጃጅና በጋሪ ሃያ ኪሎ ሜትር  ለመጓዝ እንደሚገደዱ ከነዋሪዎቹ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

 

አፋውሥኮድ ድርቅን ለመቋቀም ግንባር ቀደም ሚና ተጫውቷል

ባለፈው ዓመት በኤሊኖ ምክንያት የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም አፋውሥኮድ ግንባር ቀደም ሚና መጫወቱ ተገለጸ፡፡

የኮሪ፣ ቢዱና አፍዴራ ወረዳ ነዋሪዎች፣ ለሲፋኔ ዘጋቢ እንደገለጹት በኤሌኖ ምክንያት አምና በተከሰተው ድርቅ በወረዳዎቹ ከፍተኛ የሆነ የውሃ ችግር አጋጥሞ ነበር፡፡

የአፋር ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት /አፋውሥኮድ/ በአፋጣኝ መለስተኛ ኩሬዎችን በመቆፈርና የዝናብ ውሃ እንዲይዙ በማድረግ እንሳስቶችን ጭምር ከእልቂት መታደጉን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል፡፡

አምና የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም 31 ኩሬዎችን በመቆፍርና የዝናብ ውሃ እንዲይዙ በማድረግ የህብረተሰቡን የውሃ ችግር ለማቃለል መቻሉን የድርጅቱ ሥራ አስኪጅ አቶ አዚዝ መሀመድ ገልጸዋል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ30 በላይ ኩሬዎችን ሲገነባ በድርጅቱ ታሪክ የመጀመሪያ መሆኑንና የህብረተሰቡን የውሃ ችግር ለማቃለል አስገዳጅ ሁኔታ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አፋውሥኮድ ችግሮች ሲያገጥሙና አጣዳፊ መፍትሄ ሲያስፈልግ የተለያዩ ፕሮጀክትቶችን ፈጥኖ በማጠናቀቅ ረገድ በክልሉ መንግስትም ሆነ በሕዝቡ አመኔታ ያተረፈ መሆኑን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይመሠክራሉ፡፡

 

የሁለት ውሃ ፕሮጀክቶች ርክክብ ተደረገ

የአፋር ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት/ አፋውሥኮድ/ በዞን ሁለት እና አራት ሁለት ወረዳዎች የገነባቸውን ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለሚመለከታቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶች አስረክበ፡፡

ባለፈው ዓመት ነሀሴ  ወር አጋማሽ ርክክብ የተፈጸበማቸው ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በዞን ሁለት ዳሎልና በርሃሌ ወረዳዎች በዞን አራት ደግሞ ጉሊና ወረዳ የተገነቡ ናቸው፡፡

በዞን ሁለት  ዳሎል ወረዳ የተገነባው አይሸት ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት 350 ሺህ ሊትር ውሃ የመያዝ አቅም ያለው የውሃ ማጠራቀሚያ  ጋን የተገነባለት ሲሆን፣ በዳሎል ወረዳ አራት የገጠር ቀበሌዎች በበርሃሌ ወረዳ ደግሞ ሁለት የገጠር ቀበሌዎች ነዋሪዎችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ 12 የውሃ  ማደያና ስድስት የእንስሳት ውሃ ማጠጫ ገንዳዎች ተገንብተውለታል፡፡

በዞን አራት ጉሊና ወረዳ የተገነባው ገኑ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ደግሞ በአካባቢው ያሉ አራት የገጠር ቀበሌዎች ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፤ 250 ሺ ሊትር  የመያዝ አቅም ያለው የውሃ ማጠራቀሚያ ጋን ተገንብቶለታል፡፡

የገኑ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ስድስት የውሃ ማደያ ቦኖዎችና አራት  የእንስሳት ውሃ ማጠጫ ገንዳዎችን ያካተተ ነው፡፡

ሁለቱም ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የውሃ ችግር ባለባቸው የገጠር ቀበሌዎች በመገንባታቸው የአካባቢውን ንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር ያቃለሉ ሲሆን፤ የየወረዳዎቹ ውሃ ሀብት ጽህፈት ቤቶች ተረክበዋቸዋል፡፡

 

ትኩረት

ስኬታማ የአሥር ዓመት ጉዞ

እናቶች ውሃ ለማግኘት ረጅም ዕርቀት ለመጓዝ ይገደዱ ነበር በአፋር ክልል የተለያዩ ወረዳዎች፣ ረጅም ዕርቀት ተጉዘውና ሰውነታቸው ዝሎ ያውም ከ40 ዲግሪ ሴንትግሬድ በላይ በሆነ ሞቃታማ አካባቢ ውሃ ሳያገኙ የሚመለሱባቸው ጊዜያት በጣም በርካቶች ነበሩ፡፡ ረጅሙን ጉዞ ተጉዘው ውሃ ሳያገኙ መመለስ ብቻም አልነበረም በዚያው ለአውሬ ሲሣይ ሆነው የቀሩ  እናቶችና ወጣት ሴቶች ቁጥርም ቀላል አልነበረም፡፡

በአፋር ሴቶች ይደረስ የነበረውን እንግልትና ስቃይ የተገነዘበው የአፋር ብሔራዊ ክልል መንግሥት ምክር ቤት በውሃ ልማት ዘርፍ ሊሠራ የሚችል መንግስታዊ የልማት ድርጅት በአዋጅ ያቋቋመው በ1998 የበጀት አመት መጀመሪያ ነው፡፡

ይኸው በአዋጅ ተቋቋሞ ሥራውን በተግባር በዚያው የበጀት ዓመት የጀመረው የአፋር ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት/አፋውሥኮድ/ ሲሆን፤ እስካለፈው 2008 የበጀት ዓመት ድረስ ባሳላፋቸው 10 ዓመታት ስኬታማ ተግባራትን በማከናወን የሕዝብ አለኝታነቱን አረጋግጧል፡፡ በክልሉ በርካታ ወረዳዎች አስቸጋሪ በሆኑ የገጠር ቀበሌዎች ዘልቆ በመግባት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮችን ንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር አቃልሏል፡፡

ድርጅቱ ፈጥኖ የመጠጥ ውሃ የገነባባቸው ወረዳዎች ቀደም ሲል ፈጽሞ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ያልነበራቸው አንዳንዶቹም የአስክሬን ማጠቢያ ውሃ ስለማያገኙ አስከሬን በአፈር አጥበው የሚቀብሩ የነበሩ ናቸው፡፡

አፋውሥኮድ በአሥር ዓመታት ውጣውረድ የበዛበት ግን ደግሞ ስኬታማ ጉዞው፤ ሥር ሰድዶ ለዘመናት የቆየውን የአርበቶ አደሮች ንጹህ የመጠጥ ውሃ ቸግር  በመፍታት ለውሃ ፍላጋ ከወዲያ ወዲህ ይንከራተቱ የነበሩ አርብቶ አደር እናቶች ወጣት ሴቶች እፎይታ እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ በተለይም ወጣት  ሴቶች የትምህርት ተቋዳሽ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ለዚህም የአይሸት፣ ገኑ፣ ሂዳ ደብል፣ ኩማሜ፣ ቴሩ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚዎች ትልቅ መሣያ ናቸው፡፡

አፋውሥኮድ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ግንባታ ባካሄደባቸው ወረዳዎች የሰው ብቻ ሣይሆን የእንስሳት የውሃ ችግር ጭምር በመፍታቱ ተበታትነው ይኖሩ የነበሩ አርብቶ አደሮች በመንደር እየተሰባሰቡ የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ተቋማት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም ውሃ ባለበት ሁሉ፣ትምህርት ቤቶችና ጤና ኬላዎች አሉና፡፡

አፋውሥኮድ በክልሉ መንግሥት ም/ቤት በአዋጅ ሲቋቋም ንጹህ የመጠጥ ውሃን ለአርብቶ አደሩ ህብረተሰብ ማዳረስ ብቻ ሣይሆን የመስኖና ግጦሽ ልማትን ለማስፋፋት ጭምር ነው፡፡

ድርጅቱም ተልዕኮውን በብቃት በመወጣቱ፣የጋሶሪ መስኖና ግጦሽ ልማትን፣ የአዋድ ፣ኮካይ፤ አሊና፣ እና ታሊ ወንዞችን በመጥለፍ  በርካታ አርብቶ አደሮች ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት እንዲሸጋገሩ አድርጓል፡፡ የመስኖ ተጠቃሚ አርብቶ አደሮችም በአሁኑ ወቅት ኑሯቸው  ተሻሽሏል፡፡ ቀደም ሲል በአካባቢው የነበረው የዕርዳታ ጠባቂነት መንፈስ በከፍተኛ  ሁኔታ ቀንሷል፡፡

አፋውሥኮድ በ1998 የበጀት ዓመት ሥራ ሲጀምር ከክልሉ መንግስት  10 ሚሊዮን ብር፣ ሁለት ሃይሉክ ፒክፕ፣ ሁለት ገልባጭ መኪኖችንና አንድ የውሃ መቆፈሪያ ሪግ ለስንቅ ይዞ ነበር፡፡የአፋውሥኮድ አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ሁሉም የድርጅቱ ሠራተኞች ባደረጉት ርብርብ ድርጅቱ በአሥር ዓመት ጉዞው የህብረተሰቡን ንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር ከመፍታት  አልፎ በርካታ ተሽከርከሪዎች፣ ማሽነሪዎች፣ ገልባጭ መኪኖች፣ የራሱ የሆነ የተንጣለለ ጋራዥና ቢሮ ባለቤት ሆኗል፡፡አጠቃላይ የሀብት ክምችቱም ከ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ከትንሽ የተነሳው አፋውሥኮድም በድርጅቱ አመራሮች ባለሙያዎችና ሠራተኞች የተቀናጀ አሠራር መስዋትነት እየከፈለም ቢሆን በስኬት እየታጀበ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረሱ ሚስጥር ደግሞ የአመራሮቹ ጥበብ ፣ የባለሙያዎቹና ሠራተኞቹ ቁርጠኝነት ነው፡፡ በአሥር ዓመታት ጉዞው፣ በቴሩ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትና መንገድ ግንባታ፣ በመኪና አደጋ ምርጥ ባለሙያዎቹን በሞት ተነጥቋል፡፡ በአይሸት ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ጉድጓድ ቁፋሮ ደግሞ የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ ዋና ቆፋሪ ባለሙያው አቶ ወግሪስ ዑመር በሥራ ላይ እያለ በእባብ ተነድፎ ሕይወቱን አጥቷል፡፡የአፋውሥኮድ የአሥር ዓመት ስኬት ጣፋጭ ፍሬ ቢሆንም፣ በመራራ መስዋዕትነት የታጀበ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ያለመስዋዕትነት ድል አይገኝምና፡፡!!

 

ቅኝት

ከአርብቶ አደሮች አንደበት

በዞን ሁለት ዳሎል ወረዳ አይሸት ቀበሌ  ነዋሪ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ፋጡማ ኢበራሂም ይባላሉ፡፡ በቀበሊያቸው በአፋር ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት /አፋውሥኮድ/ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተገንብቶ የውሃ ችግራቸው ከተቃለለ ሦስት ወራትን አስቆጥሩዋል፡፡ ትልቅ የውሃ ማጠራቀሚያ ጋንን ጨምሮ የውሃ ማደያ ቦኖና የእንስሳት ውሃ ማጠጫ ገንዳ ተገንብቷል፡፡

በአፋውሥኮድ የአይሸት ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በመገንባቱ ተጠቃሚ የሆኑት ሁሉም የመንደሩ  ነዋሪዎች፣ ፊታቸው በደስታ ተሞልቷል፡፡ በሐሴት መሞላታቸውን ከፊታቸው የሚፍለቀለቀው ፈገግታ ያሳብቃል፡፡

ወ/ሮ ፋጡማ ኢበራሂም የ45 ዓመት ወይዘሮ ሲሆኑ ከታዳጊነት ዕድሚያቸው ጀምሮ እስካለፈው ዓመት ነሀሴ ወር ድረስ ውሃ ፍለጋ ሲባዝኑ ዕድሜያቸውን ገፍተዋል፡፡ ውሃ ለማግኘት በቀን ዘጠኝ ሰዓት ደርሶ መልስ መጓዝ የቅርብ ጊዜ ትዝታቸው ነው፡፡

ካለፈው ዓመት ነሀሴ ወር ወዲህ ግን የአይሸት ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶ ተጠናቅቆ ንፁህ የመጠጥ ውሃ በቀያቸው ማግኘት ችለዋል፡፡

በቀያቸው ንፁህ የመጠጥ  ውሃ በማግኘታቸው እንደገና አንደተፈጠሩ እንሚቆጥሩት ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ንፅህናው የተጠበቀ ውሃ ያውም በቀያቸው ማግኘት በመቻላቸው ደስታቸውን በቃላት ለመግልጽ ቢከብዳቸውም ፈጣሪ የሚሳነው ነገር የለምና ለዚህ አብቅቶናል፡፡ አልሃምዱሊላህ በማለት ሃሣባቸውን ደምድመዋል፡፡

ሌላኛዋ በዞን አራት የገኑ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ወ/ሮ ሀሲና ሁልቢ ናቸው፡፡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ያገኙት ልክ እንደ ወ/ሮ ፋጡማ ባለፈው ዓመት ነሀሴ ወር አጋማሽ ነው፡፡ በመንደራቸው ለእንስሳቶቻቸው ጭምር  ንፁህ የመጠጥ ውሃ በመሠራቱ የመከራ ጊዜያቸው ማብቃቱን እንዳበሠራቸው ይናገራሉ፡፡ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት በመቻላቸው ለውሃ ፍለጋ የሚያደርጉትን  ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አቁመዋል፡፡ይልቁንም ሦስት ልጆቻቸውን በገኑ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እያስተማሩ ነው፡፡የዕለት ተዕለት ሥራቸውም እንደ ከዚህ ቀደሙ ውሃ ፍለጋ መንከራተት ሳይሆን ልጆቻቸው ከትምህርት ቤት ሲመለሱ መንከባከብ ሆኑዋል፡፡

አቶ ሀንዱ ሁመድ ደግሞ በ30ዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ጎልማሣ ናቸው፡፡ በቴሩ ወረዳ ድግድጋ  ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ዕድሜ ልካቸውን ሲጠቀሙ የኖሩት በክረምት ወቅት የተጠራቀመ ንፁህናው ያልተጠበቀ የኩሬ ውሃ እንደነበር በትካዜ ያስታውሳሉ፡፡

ከ2007 ዓ.ም ወዲህ ግን አፋውሥኮድ በሠራው ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ በመሆናቸው የእርሳቸውም ሆነ የቤተሰቦቻቸው ጤንነት ተጠብቋል፤ በውሃ ወለድ በሽታ የሚጠቃም የለም፡፡ ንጽህናው ያልተጠበቀ የኩሬ ውሃ ለማግኘት አምስት ሰዓት መጓዝ  የግድ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ሀንዱ በቀያቸው ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ከቻሉ ሁለት  ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡

በአውራ ወረዳ ሂዳ ደበል የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠቃሚ የሆኑት ወ/ሮ ሀሊማ መሀሙድ ደግሞ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ከሆኑ ሁለት ዓመት አልፉዋቸዋል፡፡ አፋውሥኮድ በገነባው ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ በመሆናቸው ለውሃ ፍላጋ የሚያደርጉት ጉዞ ቀርቶላቸዋል፡፡  ለሰውም ሆነ እንስሳት ከመንደራቸው ሣይርቁ ውሃ ማግኘት ችለዋል፡፡

በሰሙ ሮቢ ገላዕሎ ወረዳ የኩማሜና ፈንቲዳ ቀበሌዎች ነዋሪ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ጉላ ቢዶ እና ሐዋ አህመድ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግራቸው ከተፈታ ድፍን አሥር ዓመት ሞልቶታል፡፡ አፋውሥኮድ ሥራ እንደጀመረ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ግንባታ ያካሄደው በእነርሱ ቀበሌ እንደሆነ ያስታውሳሉ፡፡

አፋውሥኮድ ወደ አካባቢያቸው ከመምጣቱ በፊት በርካታ የሥራ ተቋራጮች ጥናት አካሂደው ውሃ አይገኝም ብለው በመመለሳቸው ውሃ የማግኘት ተስፋቸው ተሟጦ ነበር፡፡ አፋውሥኮድ የተሟጠጠ ተስፋቸውን አለምልሞ ይኸው ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ አድርጓቸዋል፡፡ በአካባቢው በነበረው ሥር የሰደደ የውሃ ችግር አስክሬን በአፈር ይታጠብ እንደነበር ወይዘሮ ሐዋ እንባ እየተናነቃቸው ያን ክፉ ጊዜ በትካዜ ያስታውሱታል፡፡አሁን ግን ታሪክ ሆኗል፤ የውሃ ችግራቸው በአፋውሥኮድ መሠረታዊ ምላሽ በማግኘቱ፡፡

የአርብቶ አደሩን ንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት አፋውሥኮድ ባሳለፋቸው አሥር ዓመታት ስኬታማ  ተግባራትን አከናውኗል፡፡  ውሃ ተቆፍሮ ሲወጣ በመደሰት ሲታጣ ደግሞ በማዘን፤ ከአርብርቶ አደሮቹ ጋር ዕኩል ተደስቱዋል፤ ዕኩል አዝኗልም፡፡ ከሕዝቡ አብራክ የወጡት የአፋውሥኮድ አመራሮች፤ ባለሙዎችና ሠራተኞች ባደረጉት  የተቀናጀ ጥረት አርብቶ አደሮች ለድርጅቱ ያላቸው አመኔታና ክብር ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም የአፋውሥኮድ ፕሮጀክቶች በተገነቡባቸው አካባቢዎች የሲፋኔ ዜና መጽሔት ዝግጅት ክፍል ጋዜጠኞች በተንቀሳቀሱበት ወቅት ከወጣት  እስከ አዛውንት አፋውሥኮድን ደጋግመው ሲያመሰግኑ  ታዝበዋልና፡፡

መልካም ሥራ ምንግዜም ሲታወስ ይኖራልና አፋውሥኮድ ሥራ ሲጀምር ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ያደረጋቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች ውሃ በቀዱ ቁጥር የአፋውሥኮድን ስም መጥራት የተለመደ ነው፡፡ ይህም አፋውሥኮድ ባለፉት አሥር ዓመታት የሠራቸው ሥራዎች ምን ያህል ችግር ፈቺ እንደሆኑ ከአርብቶ አደሮች እንደበት ሌላ ማረጋገጫ አያሻም፡፡ የአፋውሥኮድ የአሥር ዓመት ስኬታማ ጉዞም በመጀመሪው የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ ታጅቦ ፍሬ እንዳፈራ ሁሉ የአርብቶ አደሮች አለኝታነቱን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አያጠራጥርም፡፡

አፋውሰወኮድ የአሥራ አንድ ኩሬዎች ቁፋሮ አካሄደ

የአፋር ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት /አፋውሥኮድ/ከፍተኛ የውሃ እጥረት ባለባቸው ሦስት ወረዳዎች የአሥራ አንድ ኩሬዎች ቁፋሮ ማካህዱን አስታወቀ፡፡

በድርጅቱ የኮንስተራክሽን ዳሬክቶሬት እንዳስታወቀው ባለፉት ሦስት ወራት የኩሬዎቹ ቁፋሮ የተካሄደው ከፍተኛ የውሃ እጥረት ባለባቸው ኩሪ፤ቢዱና ኤሊዳር ወረዳዎች በሚገኙ አሥር ቀበሌዎች ነው፡፡

የተቆፈሩት ኩሬዎች እያንዳንዳቸው  አሥር ሚዮን እስከ አርባ ሚሊዮን ሊትር ውሃ የመያዝ አቅመ እንዳላቸው ዳሬክቶሬቱ አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኩሬዎቹ ውሃ ይዘው ህብረተሰቡ እየተጠቀመባቸው መሆኑንና እንስሳተም በድርቁ ጉዳት ሳይደርስባቸው በአቅራቢያቸው ውሃ እያገኙ መሆኑን ዳይሬክቶሬቱ ገልጽዋል፡፡

አፋውሥኮድ ባለፈው ዓመት በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ከሰላሳ በላይ ኩሬዎችን በመቆፈር የህብረተሰቡን የውሃ ችግር በመፍታት ግንባር ቀደም ሚና መጫወቱ ይታወሳል፡፡

በሚሌ  ጊዚያዊ የእንስሳት ማቆያ እየተገነባ ነው

ሃገሪቱ ወደ ውጭ የምትልከውን  የእንስሳት ሃብት በወደብ ለማቆየት የሚወጣውን የውጭ  ምንዛሬ በማስቀረት ረገድ አይነተኛ ድርሻ የሚኖረው ጊዚያዊ የእንስሳት ማቆያ ግንባታ(ኳራንቲን) በሚሌ እየተካሄደ ነው፡፡

ግንባታውን የሚያካሂደው የአፋር ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት እንደገለጸው ባለቤትነቱ የፌደራል  እንስሳትና  አሳ ሃብት ሚኒስቴር የሆነው የእንስሳቱ ማቆያው ግንባታ እስካሁን የመሬት መደልደልና የውሃ መስመር ዝርጋታ ተከናውኗል፡፡

ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የእንስሳት ማቆያው በሃገሪቱ የመጀመሪያ ነው፡፡ከዚህ ቀደም ወደ ውጭ የሚላኩ እንስሳት የጤና ምርመራ የሚካሄደው በጅቡቲ ወደብ ነበር፡፡በዚህም የተነሳ ሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ስታወጣ ቆይታለች፡፡

ግንባታው በአሁኑ ጊዜ እየተገባደደ  ሲሆን በአጭር ጊዜ  ውስጥ ተጠናቆ አገልግት መስጠት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ለመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም  የመጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው

የአፋር ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት በተያዘው አመት የመንደር ማሰባሰብ በሚካሄድባቸው ሶስት ወረዳዎች የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እየገነባ መሆኑን ገለጸ፡፡

ግንባታው የሚካሄደው በጉሊና ወረዳ ሰበትናበተኔ እና ሰምሰም፤በዱብቲ ወረዳ ሠርዶ፤ በኤሊዳር ወረዳ አሲኢሉ ቀበሌዎች መሆኑን የድረጅቱ የዕቀድና በጀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዲማሱ ዓለማየሁ ገልጸዋል፡፡

በጉሊና ወረዳ ሰበትናበተኔ ቀበሌ የዘጠኝ ነጥብ ሁለት ሜትር መስመር ዝረጋታ አነድ መቶ አምሳ ሺህ  ሊትር ውሃ የመያዝ አቅም ያለው የውሃ ማጠራቀሚያ ግንበታ እየተካሄደ መሆኑንጠቅሰው፤በሰምሰም ቀበሌ ደግሞ ከሁለት ነጠብ ስምንት ኪሎ ሜትር በላይ  ርዝመት ያለው የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ አራት የውሃ ማደያ  ቦኖዎች፣  ሁለት የእነስሳት ማጠጫ ገነዳዎች እና አንድ መቶ ሺህ ሊትር ውሃ የሚይዝ የውሃ ማጠራቀሚያ  እየተገነቡ ናቸው፡፡

በዱብቲ ወረዳ ሠርዶ ቀበሌ እየተገነባ ያለው  የመጠጥ ውሃ አምስት ነጥብ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር የመስመር ዝረጋ፣አምስት የውሃ ማከፋፈያ ቦኖዎች፣ሁለት የእንስሳት ውሃ ማጠጫ ገንዳዎችና ሦስተ መቶ ሺህ ሊትር የመያዝ አቅም ያለው የውሃ ማጠራቀሚያ ጋን እየተሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በኤሊዳር ወረዳ ኢሲሉ ቀበሌ ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ርዘመት ያለው የውሃ መስመር እየተዘረጋ ሲሆነ፣አራት የውሃ ማደያ ቦኖዎች፤ሁለት የእነስሳተ ማጠጫ ገንዳዎችና አንድ መቶ ሺህ ሊትር ውሃ የሚይዝ የኮንክሪት ውሃ ማጠራቀሚያ እየተገነባ መሆኑን ተናገረዋል፡፡

በሦስቱም ወረዳዎች መነደር ማሰባሰብ በሚካሄድባቸው አራት ቀበሌዎች የተሙዋላ የውሃ አቅረቦት እንዲኖር ግንባታዎቹን በወቅቱ ለማጠናቀቅ አፋውሥኮድ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ከአቶ አድማሱ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Close